Madda Walabu University crest
Madda Walabu
University · Est. 2005
መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በወጣቶች ሱስ፣ አዕምሮ ጤና እና ሥነ-ተዋልዶ ዙሪያ የውይይት መድረክ አካሄደ

መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በወጣቶች ሱስ፣ አዕምሮ ጤና እና ሥነ-ተዋልዶ ዙሪያ የውይይት መድረክ አካሄደ

May 21, 2026

መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በወጣቶች እፅ ሱስ፣ አዕምሮ ጤና እና ሥነ-ተዋልዶ ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ የውይይት መድረክ አካሂዷል። መድረኩ የወጣቶችን ችግሮች በጋራ በመፍታት ጤናማና አምራች ዜጎችን ለማፍራት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።


በፕሮግራሙ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁና የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር በዛብህ ወንድሙ ወጣቶች በሀገር ግንባታ ውስጥ ያላቸውን ከፍተኛ ሚና አንስተዋል፡፡ ለዚህም የወጣቶች ጤናና ደህንነት ተጠብቆ አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ዩኒቨርሲቲው ፕሮጀክት ነድፎ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ዶ/ር በዛብህ አክለውም የችግሩ ስፋት የተቀናጀ ምላሽ እንደሚጠይቅ ጠቅሰው፣ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ተጠናክሮ በጋራ መስራት ግዴታ መሆኑን አስምረውበታል።


በመድረኩ ላይ ከሴቶችና ሕፃናት፣ ከስፖርትና ወጣቶች፣ ከጸጥታና ደህንነት፣ ከትምህርት ጽ/ቤቶችና ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችና ሌሎች ተዛማጅ አካላት የተውጣጡ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር ተሾመ ሲራክ በበኩላቸው በፕሮጀክቱ እስካሁን ስለተከናወኑ ሂደቶች ገለፃ በማድረግ፣ በቀጣይም በተቀናጀ ሁኔታ በጋራ የመስራት አስፈላጊነት በጥልቀት አንስተዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት የማህበረሰብ አገልግሎት አራት ዋና ዋና ጉዳዮችን ማዕከል አድርጎ እየሰራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂ ሽግግርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶ/ር መሐመድ ጀማል ሲሆኑ፣ እነዚህም የትምህርት ቤቶች ድጋፍ፣ ሕገ-ወጥ ስደት፣ የትራፊክ አደጋ ቅነሳ እና የወጣቶች ሱስ፣ የአዕምሮ ጤና እና ሥነ-ተዋልዶ ጉዳዮች መሆናቸውን አብራርተዋል።


ለውይይቱ መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ እና የጎባ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሪፈራል ሆስፒታል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዶ/ር አደም ኢስማኢል በበኩላቸው፣ ፕሮጀክቱ በዚህ ዙር በአራት ትምህርት ቤቶችና በሁለት የዩኒቨርሲቲው ካምፓሶች እንደሚተገበር ገልፀዋል።ከዚህም በተጨማሪ ስለችግሩ አሳሳቢነትና ጥልቀት በሰፊው አብራርተዋል፡፡

በወጣቶች ሥነ-ተዋልዶ ዙሪያ ያሉ ተግዳሮቶችና የወደፊት አቅጣጫዎችን በተመለከተ ረዳት ፕሮፌሰር ገነት ፍቃዱ ለተሳታፊዎች ሰፊ ማብራሪያ አቅርበዋል።

በመጨረሻም ተሳታፊዎች በርካታ ገንቢ ሀሳቦችና አስተያየቶችን በማቅረብ፣ ችግሩ በቅንጅትና በተባበረ እንቅስቃሴ ብቻ ሊቀረፍ እንደሚችል በመስማማት ፕሮግራሙ ተጠናቋል።


#መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ሕዝብ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ጽ/ቤት

Related Articles

View All