Madda Walabu University crest
Madda Walabu
University · Est. 2005
መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የ10 ዓመት ፍኖተ-ካርታን ከአመራሮች ውይይት በኋላ ለዘርፍ ኃላፊዎች በይፋ አስረከበ።

መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የ10 ዓመት ፍኖተ-ካርታን ከአመራሮች ውይይት በኋላ ለዘርፍ ኃላፊዎች በይፋ አስረከበ።

May 21, 2026

መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በቀጣይ ከ2018 እስከ 2027 ዓ.ም ተቋሙ የሚከተለውን አቅጣጫ ለመወሰን ያዘጋጀውን የ10 ዓመት ፍኖተ-ካርታ በተለያየ የእርከን ደረጃ ላሉ የዩኒቨርሲቲው የአመራር አካላት ( ካውንስል) በማቅረብ ሰፊ ውይይት አካሄደ።


ውይይቱ ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር፣ በምርምር፣ በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፎች በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ሊያሳካቸው የሚገቡ ግቦችን በግልጽ ለማስቀመጥ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

ውይይቱን በመክፈቻ ንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠና እንዳሉት ፍኖተ-ካርታው ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ 10 ዓመታት ከየት ወዴት እንደሚሄድ፣ የት መድረስ እንዳለበት በግልጽ የሚያመላክት ነው ያሉ ሲሆን ፍኖተ-ካርታው ተግባራዊ እንዲሆን የሁሉንም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ትጋት እና ኃላፊነት የተሞላበት ፣ ለለውጥ በቁርጠኝነት መሥራትን እንደሚጠይቅም አሳስበዋል።

በዚሁ ወቅት ፕሬዝዳንቱ የ10 ዓመት ፍኖተ-ካርታውን ለተሳታፊዎች በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን በዋና ዋና ግቦቹ፣ ተግባራዊ እቅዶቹ ፣ ስልታዊ ለውጦች ( Strategic shifts) እና የተቋሙን የወደፊት አቅጣጫ ላይ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተው ሠፊ ውይይት ተደርጎበታል።


የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ተቋማዊ ለውጥ ስራ አስፈፃሚ አቶ ደጀኔ ንጋቱ ፍኖተ-ካርታው የተዘጋጀበትን ሂደት እና የመጀመሪያ ምዕራፍ እቅድ ለተሳታፊዎች በዝርዝር አቅርበው ከተሳታፊዎች ገንቢ ሃሳቦችን እና አስተያየቶችን ተሠጥተውበት የጋራ ተደርጓል። 

ከውይይቱ በኋላ ፕሬዝዳንቱ ከሁለቱ ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣የመወዩ የጎባ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ሻሸመኔ ካምፓስ እና ከፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ ጋር የ10 ዓመት ፍኖተ-ካርታውን በይፋ ተፈራርመው ተረካክበዋል። ይህም ዩኒቨርሲቲው ወደ ተሻለ ተቋማዊ እድገት ለመሸጋገር እየወሰደ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ እርምጃ መሆኑ ተጠቅሷል።

በመጨረሻም የ10 ዓመት ፍኖተ-ካርታው ዕውን እንዲሆን በኮሚቴ አባልነት ለተሳተፉ አካላት የዕውቅና ሰርቲፍኬት ተበርክቶ መርሃ ግብሩ ተጠናቋል።


#መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ጽ/ቤት

Related Articles

View All